News News
Minimize Maximize
« Back

በጥንካሬዋ የአንበሳ ስያሜ ያገኘች ከተማ ሲንጋፖር

 

በደቡብ ምስራቅ እስያ አንዲት እጅግ በጣም አስገራሚ የሆነችና ከአለማችን ከተሞች ራስዋን ማስተዳደር የቻለች ብቸኛ ከተማ ትገኛለች፡፡ ከተማዋ ለረጅም አመታት ለአካባቢው ነዋሪዎች እንደልዩ መገለጫ ሆኖ በቆየውና የእንስሶች ንጉስ በሆነው አንበሳ ስም ትጠራለች፡፡ ለዚህም ይመስላል በአካባቢው በሚነገረው ቋንቋ ሲመሃፑራ ወይም ባሁኑ አጠራር ሲንጋፖር ተብላ የተጠራችው፡፡ ትርጉሙም አንበሳ ከተማ ማለት ነው፡፡

(Siṃhapura; siṃha is "lion", pura is "town" or "city").

ከተማዋ በበርካታ ደሴቶች ጥምረት የተመሰረተች ናት፡፡ የምትገኘውም አሩቅ ምስራቅ ሲሆን ማሌዥያን በስተሰሜን ኢንዶኔዢያን ደግሞ በስተደቡብ ታዋስናለች፡፡

ሲንጋፖር ከተማ አመሰራረት በርካታ ምሁራን አሁንም ክርክር የሚያደርጉ ሲሆን ነገር ግን ብዙዎቹ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መመስረቷን ይስማማሉ፡፡ በተለያዩ አመታትም እንደፖርቹጋል፣ ቻይናና እንግሊዝ ባሉ ሀገራት ለረጅም አመት በቅኝ ግዛት ስትተዳደር ቆይታለች፡፡ ለመጀመሪያ ግዜም ራሳቸውን ማስተዳደር የጀመሩት እ/ኤ/አ በ1959 ነበር፡፡

ሲንጋፖር በደሴቶች ላይ የተቆረቆረች ከተማ ናት ማለት ይቻላል፡፡ እስካሁን ባጠቃላይ 65 ደሴቶች በስሯ ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ ደሴቶችም ጠንካራ የከተማ አስተዳደር መመስረት ችለዋል፡፡ በተለይም በከተማዋ በነበረው ከፍተኛ የከተሞች መስፋፋት ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሀገሪቱን የተፈጥሮ ደን አሳጥቷታል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ችግር ለመቅረፍ በወሰዱት እርምጃ የከተሞች መስፋፋትና እድገት ጎን ለጎን በእያንዳንዱ ደሴት 10 በመቶ የሚሆነው ቦታ ለአረንጓዴ ስፍራና ፓረኮች አገልግሎት እንዲውል ተደርጓል፡፡ በዚህም ሰፊ ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን እ/ኤ/አ 2014 በተካሄደው አለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ጥናት ከአለም ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ ነድፈው ውጤት ካስመዘገቡ ሀገራት የአራተኛ ደረጃን ማግኘት ችለዋል፡፡

መኖሪያ ቤት

በሲንጋፖር የቤት ልማት ፕሮግራም የተጀመረው እ/ኤ/አ በ1940ዎቹ ነው፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ ከተሞችም ከአለማችን እጅግ በጣም ስኬታማ የሆነ የቤቶች ልማት ስትራተጂ ተግባራዊ ካደረጉ ከተሞች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የቤቶች ፕሮግራም ከተጀመረበት ግዜ አንስቶ ባሉት አመታት ለ1 ሚሊዮን በላይ ቤቶችን ገንብተዋል፡፡ በዚህም ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚቻል መልኩ የህብረተሰብ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ መመለሳቸውን ነው፡፡ በሲንጋፖር ከተሞች በየቦታው ለአይን በሚያታክት መልኩ የተገነቡት ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ለከተሞቻቸው ስኬት ትልቅ ማሳያ መሆናቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

ሀገሪቱ ለመጀመሪያ ግዜ በከተሞቿ የቤት ፕሮግራሞች ነድፋ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችው እ/ኤ/አ በ1947 ነበር፡፡ ፕሮግራም ከተነደፈ በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ተገንብቶ ከተላለፉ ቤቶች መካከል ከ1947 እስከ 1962 ባሉት 15 አመታት ከ50 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተው ለህዝቡ ተላልፈው ነበር፡፡  ይሁን እንጂ በወቅቱ ከነብረው የህዝብ ቁጥር አንፃር (1.3 ሚሊዮን) ይህ ነው ሊባል በሚች መልኩ የህብረተሰቡን የቤት ጥያቄ መመለስ አልቻለም ነበር፡፡

 በዚህም ምክንያት በዘርፉ በነበሩ ፖሊሲዎች ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ በዘርፉ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ተቋረጮች ወደዘርፉ ገብተው እንዲሰሩ ተደርጓል፡፡ በዚህም በጣም አመርቂ የሚባል ለውጥ ማምጣት የተቻለ ሲሆን በ50 አመታት ውጥም ከ1 ሚሊዮን በላይ ቤቶችን በመገንባት በሀገሪቱ በነበሩ ከተሞች የነበረውን የቤት ችግር ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ ችለዋል፡፡ የተገነቡት ህንፃዎቹ አብዛኞቹ ከ25 ፎቅ በላይ እርዝማኔ አላቸው፡፡

ለህንፃቹ የፀሀይ ብረሀን እንዲያስገቡ ታስቦ የተሰሩት ትላልቅ መስኮቶች ልህንፃዎቹ ልዩ ውበት ሰጥቷቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ህንፃዎች በአማካኝ ከ5 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ይይዛሉ፡፡ አንዳንዶቹ ህንፃዎች ወደ 10 ሺህ የሚጠጋ ነዋሪዎችን የሚይዙም አልጠፉም፡፡ ከ97 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሀገሪቱ ዜጎች ሙሉ ለሙሉ የመሰረተ ልማት አቅርቦት በተሟላለት ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ መኖሪያዎቹ ሙሉ ለሙሉ ኢንተርኔትን ጨምሮ የመሰረተ ልማት አገልግሎት የተሟላላቸው ናቸው፡፡ በቅርብ አመታት የተገነቡት ህንፃዎች ስፖርት ማዘውተሪያ (ጂም)፣ መዋኛ ገንዳ፣ ከህንፃው ስር የመኪና ማቆሚያ ቦታ ያላቸው ናቸው፡፡ የፀጥታ ጉዳይም ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡

ኢኮኖሚ በውጭ ግብይት፣ በንግድ ማእከልነት፣ ከአለማችን በግዝፈቱ የሚታወቀው የነዳጅ ማጣሪያና መሸጫ፣ ግዙፉ የመርከብ ጥገና እና እድሳት ተቋም እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ስራዎች ግዙፍ ካፒታል ከሚንቀሳቀስባቸው ተቋማት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ሀገሪቱ ከአለማችን ሀገራት ሲበዛ ለንግድ ምቹ ከሚባሉ አገራት ተርታ ትመደባለች፡፡ ነፃ የኢኮኖሚ ስርአትን ተግባራዊ ካደረጉ ሀገራትም የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች፡፡ ሆንኮንግ፣ ደቡብ ኮሪያና ታይዋንን ጨምሮ ከሌሎች በርካታ ሀገራት ጋር ጠንካራ የንግድ ግንኙነት አላት፡፡ በዚህም ላለፉት 40 አመታት ከ5 ያላነሰ አመታዊ እድገት ስታስመዘግብ ቆይታለች፡፡ ሀገሪቱ በከተሞች መልካም አስተዳደር ዙሪያ ባወጣችው እስከሞት ቅጣት በሚደርስ ጠንካራ ህግ ከሙስና የፀዳና የብዙዎችን ጥያቄ ባመከለ መልኩ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ ህግ አላት፡፡ በዚህም ሀገሪቱ በተነፃፃሪ ከሙስና የፀዱ ሀገራት ማለትም ከኒውዜላንድ እና እስካንዲኔቪያን ሀገራት ቀጥሎ ስሟ በስፋት አብሮ ይነሳል፡፡

ከተማዋ በዘረጋችው ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ፣ ባሏት ምቹ ወደቦች፣ የተማረ የሰው ሀይል፣ መሰረታዊ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና በሙስና ላይ የማያዳግም እርምጃ ከመውሰድ የማያመነታው ህጋቸው ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አድርጓቸዋል፡፡ በተለይም ደግሞ በከተማዋ በኢንቨስትመንት ለማልማት ለሚገቡ ኢንቨስተሮች እጅግ በጣም ቀላል የሆነ የታክስ ክፍያ ብዙዎች ወደ ሀገሪቱ ገብተው እንዲያለሙ በር ከፍቷል፡፡ 

ባሁኑ ወቅት ባጠቃላይ ከ10 ሺህ በላይ የአሜሪካ፣ የጃፓን፣ የቻይና፣ የህንድ እና የአውሮፓ ህብረ ብሄራዊ ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡ በዚህም እቃዎች ለንግድ ወደ ውጭ በመላክ በአለም 14ኛ፣ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ደግሞ የ15ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ የ2017 የአለማችን የገንዘብ ተቋም ሪፖርት እንደሚያሳየውም የገሪቱ የነብስ ወከፍ ገቢ ከ400 ቢሊዮን በልጧል፡፡ ይህም ሀገሪቱ ካላት የህዝብ ቁጥር (5.4 ሚሊዮን) ጋር ሲነፃጸር ቀላል የሚባል ደረጃ አደለም፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች አመታዊ የነብስ ወከፍ ገቢም 75 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ደርሷል፡፡ ይህም በአለማችን እጅግ በጣም ካደጉ ሀገራት ተርታ ይመደባል፡፡

 ሲንጋፖር የሀባታሞች ከተማ ናት ማለት ይቻላል፡፡ በአለማችን ታዋቂው የማህበራዊ ድረገፅ ፈጣሪው ማርክ ዛከርበርግን ጨምሮ የበርካታ የአለማችን ቢሊየነሮች መኖሪያ ናት፡፡ አሁን ባለው መረጃ በዚህች ሀገር የሚኖሩት ሚሊየነሮች በሌሎች የአለማችን ሀገራት ከሚገኙ ሚሊየነሮች በእጅጉ ይበልጣል፡፡ በጣም የሚያስገርመውም በሀገሪቱ ከሚገኙ 6 ዜጎች ቢያንስ አንዱ ከ1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የማያንስ ሀብት ባለቤት ነው፡፡

የስራ እድል ፈጠራ አገሪቱ በተለይም በከተሞች የስራ እድል ፈጠራ ዘረፍ እጅግ ስኬታማ ናቸው ተብለው ከሚቀመጡ ሀገራት ተርታ ትገኛለች፡፡ ከአለማችን ሀገራትም ዝቅጠኛ የስራ አጥ ቁጥር ያላጥ ሀገር ናት፡፡ አለማችን በታላቅ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በወደቀችበት ባለፉት 10 አመታት እንኳ የሀገሪቱ የስራ አጥ ቁጥር ከ3 እና 4 በመቶ አለበለጠም ነበር፡፡ የቅርብ ግዜ መረጃዎችን ሰንመለከት ደግሞ አሁን ያለው የስራ አጥ ቁጥር ከ2 በመቶ አይበልጥም፡፡

ከስራ እድል ፈጠራው ጎን ለጎንም ነፃ የህክምናና የትምህርት አገልግሎት፣ ለአቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ደሞዝን ጨምሮ ወሊድን ለማበረታታት አንድ ልጅ ለወለዱ ዜጎች 166 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ስጦታ ይሰጣሉ፡፡ በተጨማሪም ነፃ የምግብና መሰል ፍላጎቶች አቅርቦትና መጓጓዣም ከነዚህ ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ 

ጤና ሲንጋፖር ሙሉ ለሙሉ የጤና ሽፋን ተደራሽ የደረገች ሀገር ናት፡፡ በዚህም በአለማችን የ4ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ አብዛኛው የሀገሪቱ ህዝብም የሚታከመው በነፃ ነው፡፡ በአለማችንም ዝቅተኛ የህፃናት ሞት የሚመዘገብባት ሀገር ናት፡፡ በአለማችን ረጅም እድሜ ከሚኖርባቸው ሀገራትም እንዲሁ በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በሀገሪቱ በተዘረጋው የጤና መድህን ዋስት የሚሰበሰው ብርም ከ85 በመቶ በላይ አቅም የሌላቸው ዜጎችን የህክምና ወጪ ይሸፍናል፡፡

ጂዎግራፊያዊ አቀማመጥ

ሀገሪቱ በሰሜን ምእራብ የሀገሪቱ ክፍል የምትገኝ ሲሆን የቆዳ ስፋቷም 130 ስኩኤር ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ባጠቃላይም ከ63 በላይ ደሴቶች አሉ፡፡

ፅዳት በሀገሪቱ የሚገኙ ከተሞች ለፅዳት ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡  በተለይም ለመላው የሀገሪቱ ነዋሪ ስለፅዳት ጠቀሜታ ሰፊ የሆነ ግንዛቤ ለመፍጠር የተለያዩ ስትራተጂዎችን ተግባራዊ አድርገው ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ በአለማችን እጅግ በጣም ንፁህ የሚባሉ ከተሞችም የሚገኙት በዚች ሀገር ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በከተሞቻቸው መንገዶች ላይ የከረሜላ መጠቅላያ እንኳ መሬት ላይ መጣል ሲበዛ ነውር የሆነው፡፡ ከባድ ለሆነ ቅጣትም ይዳርጋል፡፡ በተጨማሪም በዘመናዊ ማሽኖች በቀን በቀን ከተሞቻቸው ይፀዳሉ፡፡

የአየር ንብረት የከተማዋን የአየር ንብረት ስንመለከት ከተማዋ ለምድር ወገብ የቀረበች እንደመሆኗ አመቱን ሙሉ ተመሳሳይ የአየር ፀባይ ታስተናግዳለች፡፡ በብዛት እርጥበት አዘል አየር ያላት ሲሆን አመቱን ሙሉ ዝናብ አለ፡፡ የከተማዋ የሙቀት መጠንም ከፍተኛ 35 ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ 20 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ነው፡፡

 የህዝብ ቁጥር በአሁኑ ወቅት 5.5 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በዚህች ሀገር ይኖራል፡፡ ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥሯም ወደ 45 በመቶ የሚጠጋው የውጭ ዜጋ ነው፡፡ ሀገሪቱ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻና ግዙፍ አለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ከተማዋ ለኑሮ ውድ ከሚባሉ ከተሞች ተርታ እየተሰለፈች በመምጣትዋ ብዙዎቹ ነዋሪዎቿ ስራቸውን በዚህች ሀገር ቢያደርጉም ቤታቸውን ባጎራባች ደሴቶች ለማድረግ ተገደዋል፡፡ ይህም የከተሞች የህዝብ ቁጥር ጋብ እንዲል አድርጎታል፡፡

ሀይማኖት በሀገሪቱ ብዙውን ቁጥር የሚይዙት የቡዲዝምና የክርስትናና እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እስልምና ሂንዱይዝምና ሌሎች ሀገረሰባዊ እምነት ተከታይ ዜጎች በሀገሪቱ ይገኛሉ፡፡

ማጠቃለያ

ከተማዋ በማራኪ ደሴቶች የተመሰረተች መሆኗ ልዩ ውበት ሰጥቷታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከተማዋ በአለማችን ውብ ከሚባሉ ከተሞች የ11ኛን ደረጃ ይዛለች፡፡ በጥብቅ ደን እንዲሁም በብሄራዊ ፓርኮች ላይ ሰፊ ስራ በመስራታቸው በአለማችን ብዙ ቁጥር ያለው ጎብኚዎችን በየአመቱ ያስተናግዳሉ፡፡ የሀገሪቱን ታሪክ እንዲያፀባርቁ ተደርገው የተገነቡት ውብ ሰማይጠቀስ ህንፃዎች እና የሌሎች በርካታ ኪናዊ መስእቦች ባለቤት ናት፡፡ በአለማችን ብዙ ቱሪስት ከሚጎርፍባቸው ከተሞች የ10ኛ ደረጃ ስትይዝ ከቱሪዝም የምታገኘው ገቢ ደግሞ ከአለም የ8ኛን ደረጃ ይዟል፡፡ ለአብነት ያክል እ/ኤ/አ በ2015 ብቻ ከ3 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች ከተማዋን ጎብኝተዋል፡፡ ሲነጋፖር ከተማ በጥቂቱ ይህን ትመስላለች፡፡ በቀጣይ የጋናዋን እርሰ መዲና ሉዋንዳን እናስተዋውቃቹሀለን፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

በካሳሁን ገ/መድህን